Pages

Monday, 6 May 2013

የመንደሩ አንግዳ


ክፍል 1


   አዚህ ቤቴ በራፍ ላይ ሆኘ አካባቢውን ስቃኘው ለኔ ብቻ የታወቀኝ አዲስ ስሜት ይሰማኛል።ተሽከርካሪው፣መንገደኛው--- አንዲሁ ሲተራመስ አያለሁ።ከላይ ታች ከታች አላይ የሚንቀሳቀስ ነገር ብቻ ይታየኛል።---አዎ አንደኔ የምቆዝሙ ሞልተው።ከግቢዬ ፊትለፊት ያለው መንገድ ተሻግሮ ከቦዩ አጠገብ የሸበትና የሸመገለ የዝግባ ዛፍ ተገትሮ የለ!ከኔ በምን ይሻላል? በምንም ---ግን ብዙዎች የከሰአቱን የሃሩር ፀሐይ ስለሚጠለሉበት ይወዱት ይሆናል።የሚወዱት ግን አንደሊቀ መላአኩ ክንፍ ቅርንጫፉን ዘርግቶ ከንዳድ ስለጠበቃቸው ሊሆንም ይችላል።

 አኔ ግን ሁልጊዜ ከቤቴ በረንዳ ላይ ሁኘ አተኩሬ ስመለከተው አቆያለሁ።ንፋስ ሽው ሲል---ሲፈነጥዝና ሲደንስ አብሬው ስወዛወዝ ፈርቼ ይሁን አፍሬ ባላውቀውም ሰው አየኝ አላየኝ አያልኩ ፊቴን አዞራለሁ።ግን ብደሰት ምን ቸገራቸው---ከነሱ ገድ ጨልፌ አልወሰድኩ።
  ከስራ ወደ ቤት ---ከቤት ደግሞ ወደ ሥራ ሲሄዱ አዚሁ ዛፍ ስር ያርፋሉ።መቀመጫ አበጅተው ጀርባቸውን ወደ'ኔ ግቢ አዙረው ይቀመጣሉ።አኔ ከመንገደኞቹ ጀርባ ሳይሆን ሰማይ ለመንካት ከሚንጠራራው የዝግባ ዛፍ ልቤ ጥፍት ይላል።
  ቤት ድረስ የሚመጣው የልብ ወዳጄ ቢኖር ተሾመ ብቻ ነው።ጉዋደኛዬ ስለሆነ።አያንዳንዱን አመሌን በደንብ ስለሚያውቅ "ምን አያደርክ ነው?"አይለኝም።አሱ ጎበዝ ልጅ ነው።ጉብዝናው ግን ዘወትር በሚሞነጫጭረው የደብተሩ አርሻ ላይ የግጥምና የልቦለድ መስክ ሲኮተኩት ብቻ ነው።ታሪክ መፃፍ ይወዳል።ገጠመኞችን ማስታወሻ መያዝ ያስደስተዋል።መፃፍ---መፃፍ---በቃ አየፃፉ መኖር።ፅህፈት "የሕይወቴ ጥሪ"ነች ማለት ያበዛል።
  ስአል ይወዳል አንጂ አይስልም።አንዳንዴ ቤቴ በረንዳ ላይ ሆኘ ወንበር ላይ በመቀመጥ አላፊ አግዳሚው ሳማትር ያይና ---
     'ፈላስፋው' ይልኛል።ምንም ስፈላሰፍ አላየም።አንዲሁ ነው።
     'መመሰጥ ብቻ አይደለም።ራስህን አታስጨንቅ።' ሲያወራ አይታክተው።
     'የውስጥህን ተንፍሰው።ፃፍ---ብዬሀለው ፃፍ የውስጥህን ጩሀት' ይለኛል።

  ተሾመ የምሩን ነው የሚያወራኝ።በተለምዶ ዝምታዬ ዝም አልኩ።ከቀኑ 7:00 ሆነ።የድብርት ስሜት አየተሰማኝ ነው።ቅርቅር የሚለኝ ነገር ውስጤ ሲማሰል ይታወቀኛል።ሌላ ቀን አንዲህ በሰንበት አንደወየበ ነጠላ ፊቴ ደብዝዞ አያውቅም።ቀኑ ደስ አይልም።ሳላውቀው ሰዓቱ አያዘገመ ነው።ፀሐይ ቁልቁል አዘቅዝቃለች።ተነስቼ ወደ ውስጥ ገባሁ።ወደ ውስጥ ስዘልቅ በአብዛኛው አራሴው ከሳልኩዋቸው ስአሎች ተፋጠጥኩ።አይኖቼ አያንከራተትኩ ተመለከትኩ።ከስነ-ጥበብ ት/ቤት ከተመረቅኩ በሁዋላ ጥቂት ስአሎች ሸራ ላይ ለማኖር ሞክሬ ነበር።በመጠኑ ተሳክቶልኛል።በአብዛኛው በሀገራችን ኪነ ጥበብ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ምሁራንን ምስል ነበር የምስለው ።አጅግ ጥበብ አፍቃሪ ነኝ።ሙዚቃ፣ግጥም፣ወግ ልቦልድና ሌሎችም በሰአል ቢሆኑ የበለጠ የሚያምሩ ይመስለኛል።በየግድግዳው የሰቀልኩዋቸው ሰአሎች አንዴ ፀአዳ ፈክተው ከውጭ ለሚገባ አንግዳ አይን ጠልፎ የሚያስቀር አንዳች ኃይል አላቸው።ወደ ውስጥ በሚያስገባው በር መቃ ከፍ ብሎ የሎሬት ፀጋዬ ገ- ፎቶ ያረፈበት ሸራ በመጠኑ ውይቦ ተሰቅሏል።ሎሬት ፀጋዬ የጥበብ ብቃቱ፣የቅኔው ጥልቀቱ፣የግጥም ምጥቀቱ አጅግ አደንቅለታለሁ።
 
ቀጥሎ ያለው መኝታ ክፍሌ ነው።'በድርሰቶችና በስአል የታጨቀ አስገራሚ ሙዚየም'ይለዋል ተሾመ።ከአልጋዬ ራስጌ ያንጠለጠልኩት ሰአል ገና አንደገባሁ አንፋጠጣለን።በትምህርት ቤቶች መሃከል በተካሄደ ውድድር ያሸነፍኩበት አብስትራክት ነው።ያምራል።ባብዛኛው ግድግዳ ላይ የነ በዓሉግ ፣ጋሽ ፀጋዬ ገ፣ጋሽ ስብሐት ገ፣ዶ/ር ሐዲስ አ ና ዳኛቸው ወርቁ የመሳሰሉ ጥበበኞች አጅግ አምረው ይታያሉ።ከቁም ሳጥኑ አጠገብ ያለው መደርደርያ የትውልድ ዓይን የሚገልጡ የጥበብ ስራዎች የታጨቀበት የጥበብ አምባ ነው።ዛሬ አንዴት አንደሆነ በማላውቀው ስሜት ምንም ስአል የመሳል ፍላጎት ቀዘቀዘብኝ።ምን ሆኘ ነው?

ከአልጋዬ ፊትለፊት የወጠርኩት ሸራ ላይ ጅምር ስራዬ ለመቀጠል ፈለግኩ።አጅግ የማደንቀው ደራሲ፣ጋዜጠኛና አሳቢ ምስሉን ለማስቀመጥ መጣሬ ነው።ፀሐይ በደመና መሃል አንገቱዋን ቀና አድርጋ ስትታይ የተገመጠ ማንጎ ትመስላለች።ሰማይ ጥቁርና ግርጫ ካባ ደርባለች።ኩርፍያዋን የምያደምቁላት የመብረቅ ብልጭታ ቤቴ ገብቶ የሎሬት ፀጋዬ ምስል ላይ አንደግርፋት ሰምበር ያሳርፍበታል።

  የተለያዩ ቀለማትና ብሩሾች አቀራረብኩና አልጋው ጠርዝ ላይ ቁጭ አልኩ።በሃሳብ ማጥ ውስጥ ተዘፈኩ።ብሩሹን ነክሬ ሸራው ላይ ልቀባ ስል የሆነ ነገር ያዝ አደረገኝ።ከራሴ ታገልኩ።ራስ ምታት ያታድፈኝ ጀመር።ደመና ለንቦቿን ጥላለች።አየመሸ አንደሆነ ያስታውቃል።ተነስቼ የተደረደሩት የደራሲው ስራዎች በአግራሞት ተመለከትክዋቸው።ስለደራሲው ካየሁትና ከሰማሁት የሚመጣልኝን ምስል ተወሳሰበብኝ።ነገር ግን ይመጥነዋል ብዬ ባመንኩበት ንድፍ አየሰራሁት ነው።አሁንም አይኖቼ ከኚህ አውቅ ደራሲ ስራዎች መንቀል አልቻልኩም።---ከቆይታ በሁዋላ የስአሉ ነገር አየከበደኝ ሲመጣ የሳልኩትን ያህል ብቻ በሚያምር ሁኔታ ከልቦለዶች በላይ ሰቀልኩት።አኚህ ስራዎች በቁጣ የገረመሙኝ መሰለኝ።ልክ ገላቸው ንዝረት አንዳለው ነገር ሲያርቀኝ፣ደማቸው በበቀል አንደሚንቀለቀል ሆኖ ታየኝ።  ግን ለምን ? የምሆነው አላውቅም ---በድካም የዛለው ሰውነቴ አልጋው ላይ ዘረገፍኩት።የያዝኩት ብሩሽ  አጨማለቀው።መነሳት ቀፈፈኝ።ከዉጭ ነጎድጉአድ በሚያስገመግም ድምፅ ያስፈራራኛል።ወደ ተሾመ ልደውል አሰብኩና ተውኩት።ተንጋልዬ አልጋዬ ላይ ወደቅኩ።ፍርሃት አጥንቴ ድረስ ሰርስሮ አየገባ ይጠዘጥዘኛል።የአይኞቼ ቆብ አቅላቸውን አጥተው ተዝለፍልፈዋል።ክፍሉ ዝምታ ብቻ ሆነ።  በነጎድጉዋድ የታጀበው ዝናብ ሳያቁዋርጥ ሿ ሿ ሿ ሿ ሿ ሿ አያለ ነው።አንዳች መንፈስ በሰማይ መብረቅ ተመስሎ አንዴጭልፊት ነፍሴን መንጭቆ ሊወስድ ታገለኝ።አኔም አቃተኝ።አጅ ሰጠሁ።


ከፍል 2
   
    
ሁሉም ነገር አየተወሳሰበብኝ ነው።ሰው ምን ነክቶት ነው?ባወራው  አያወራኝ ---ብጠይቅ አይመልስልኝም?ሁኔታው ለማወቅ መንገዱ ይዤ ስወርድ አንድ አባት አገኘሁቸው።
'ምነው አባት?ምን ተፈጠረ ?ይህ ሁሉ ሰው ወዴት ነው የሚጎርፈው?' ጥለውኝ ሄዱ።ያዘኑ ይመስላሉ።ዙርያ ገባውን ብመለከት የሚያስገርም ተፈጥሮ ነው።በብዛት የሚርመሰመስ ሕዝብ ይታየኛል።ኮርብታ ላይ ወጣሁ።ከዚያም ኮረብታውን ቁልቁል ስወርደው  ያሞከሞከው አግሬ መሄድ አቃተው።የውስጥ አግሬ በድንጋይ አየታረሰ ፍም መስሉዋል።የዘወትር ብሩሼን አንደያዝኩ ነው።ግን ባልይዘውስ ?

    አንዴ ዉሻ አያለከለኩኝ ከኮረብታው ወጣሁ።የሚያስደንቅ ነገር አየሁ።በርከት ትልቅ ወንዝ አኩል የሚከፍላቸው ሁለት መንደሮች ታዩኝ።ፍፁ ተቃራኒ ገፅታ ያላቸው።በአንደኛው ሳቅ፣ደስታ፣---በሌላኛው ሃዘን፣ለቅሶ  ይታየኛል።ያሉበት ለመድረስ የማይቻል ነው።ውስጤ ጩህ ጩህ ይለኛል።ድምፄን ከፍ አድርጌ ልጣራ ስንጠራራ---
'ተው አንጂ ---ይቅርብህ ባትጮህ ይሻላል'የሚል አንደ ሐር የለሰለሰ ድምፅ ከጀርባዬ ሰማሁ።በድንጋጤ ዘወር ስል ከትልቅ ድንጋይ ስር ትልቅ አርግብ አየሁ። በጣም ትልቅ ናት።ግራ ተጋብቼ አይኔ ግራና ቀኝ ሳንከራትት
                     'አየህ' አለችኝ በአግሩዋ ወደ ሁለቱ መንትያ መንደሮች አያመለከተች።
                      'አሁን የሚሆነውን ተረጋግተህ ጠብቅ' ስትለኝ---
                      'ምኑን ነው የምጠብቀው?' አልኩዋት።  
                      'ይታይሃል መንደሮቹ ጋ በግራ በኩል ባለው አዝነው ተክዘው--- ደግሞ በቀኝ በኩል ደስተኞች    ብቻ የሰፈሩባት ነች።' ማውራቱዋን አልቆመችም።
'ይህን ሁል የረበሼ ነገር አውቀዋለሁ።አንተዋወቃለን።አንተም አውቅህ ይሆናል ።ለማንኛውም ኮረብታው ላይ ሆነህ የሚፈጠረውን ጠብቅ።'
ጭራሽ ጤንነቴን አየተራጠርኩ ወደ ኮረብታው ወጥቼ መንትያ መንደሮቹን ቃኘሁ።በአንደግኗ መንደር መሃል ለመሃል የሚያቁዋርጡ መንገዶች በሰውና በመኪና ተሞልተዋል።ይራወጣሉ።አቃ አንደጣለ ሰው ይንከራተታሉ።አርስ በርሳቸው አየተገፈታተሩ ነው የሚሄዱት።ሁሉም ስጋት ውስጥ አንደሆኑ ነው የሚያሳብቅባቸው።የመንደሩ አውራ ጎዳናዎች በፈዘዘ ብርሃን ተውጠዋል።ከርቀት ስለሆንኩ ማንም  መለየት አይቻለኝም።ከሰማይ የዝናብ ዶፍ አየወረደ ነው።ሁሉም (ከኔ በስተቀር )አየዘነበ አንደሆነ ልብ ያሉት አይመስሉም።በብርድ የደረቁ ጣቶቼ ቁዋንጣ መስለዋል።ድንገት በመንደሩ መሃል በብዙ ሰው የተከበበ ሠርገላ ታየኝ።አንደ አፄዎቹ ሰርገላ።
       'ይህ ሁሉ ሕዝብ የሚተመው ወድዚያ ነው?' አልኩኝ በሃሳቤ።ኮርብታው ፈራሁት ።ብቻዬ ነኝ።
       'የንግስና ስነስርዓት ይሆን አንዴ?'አላለሁ።
ፈዘዝ ብዬ አንዳለሁ አርግብቷ አጠገቤ መጥታ ስትቆም ከሃሳቤ አናጠበችኝ።አሷም በጣም አዝናለች።አንባዋ ሰናፍጭ ከሚያክል አይኑዋ ወጥቶ ዱብ ሲል ይሰማኛል።ዝናቡ አስካሁን አላባራም።አደገኛ የመብረቅ ድምፅ          አካባቢው አናወጠው።የሚያለቅሱ -----የሚነፋረቁ ብዙ ድምፆች አሉ።


በሁለቱ መንደሮች የሚሆነው ፍፁም ተቃራኒ ገፅታ (ሃዘን፣ደስታ)አጅግ  ይገርማል።መሀላቸው የሚያልፈው ወንዝ አቤት ሲያስፈራ ---አርግብቷ ግን አንባ በአንባ ሆናለች።አካሏ ተዝለፍልፎ ላባዎቿ የተነቃቀሉ መሰለኝ።
              'ለምን የምታውቂውን አትነግሪኝም?'በሚለማመጥ ድምፀት።ቀና ብላ አየችኝ።
              'አሱን ብሩሽ ለምን ያዝከው ?'አንባዋ አየጠራረገች ።
               'ሥራ አየሰራሁ ነበር። የጀመርኩት ሳልጨርስ ---'ቃል አጠረኝ ።
               'ሂድ ጨርሰህ ስትመጣ ሁሉንም አነግርሃለሁ።' ስትለኝ ንደቴ መቆጣጠር  አልቻልኩም።የስድብ ዶፍ አዘንብኩባት።
               'አኔም አንተም  ወዳጆች አንደሆንን ታውቃለህ?'
               'የት ነው የማውቅሽ?በፍፁም የማውቀው ሰው አረሳም ።'ቀጠልኩና
               'ግን አንቺ ማነሽ?'አልኩዋት።በጨዋነት ለዛ።
               'አኔ ?'
               'አው'
               አኔ አኮ ጥበብ ነኝ።' አለችና ክንፏን አየመታች ተነስታ ከአይታዬ ተሰወረች።ከአንዲት መድብ አረፍ አልኩና ጋደም ስል ከሰማየ ሰማያት የተላከ የመብረቅ ድምፅ ከጥልቁ የ ህልሜ ዓለም መንጭቆ አወጣኝ።ተንቀጠቀጥኩ።ይህን ሁሉ በህልም ሆን ብሎ ማሰብ አቃተኝ።የንጋት ወፎች ሲዘምሩ ይሰማኛል።ፊቴ ላይ ላብ ብቻ ሆነ።ማታ በወደቅኩበት መሆኔን የያቁት ብሩሽ ሳየው ነው ያወኩት።ብድግ ብዬ መደርደርያው  ስመለከት ማታ የሰቀልኩት ስአል ወድቆ አገኘሁት።
ልብሴ ለባበስኩና ደጅ ስወጣ ብዙ ሰው ነጠላውን አየተከናነበ ወደ ስላሴ ቤተ/ክርስትያን ይነጉዳል።ወደ ተሾመ ስደውል ስልኩ አይነሳም።ቤቴን ዘግቼ ወደ ስላሴ የሚወስደውን መንገድ መግዋዝ ጀመርኩ።ከመንገዱ ዳር ከሻይ ቤት የሚሰማውን የጠዋት ዜና ጆሮዬ ጠለፈኝ።ቆምኩ።
                "ዜና አረፍት---በኢትዮጵያ የአማርኛ ስነፅሁፍ ዘርፍ ጉልህ ድርሻ ከነበራቸው ደራስያን መሃከል በጋዜጠኝነት፣በአርታኢነት፣በመምህርነትና በደራሲነት የምናውቀው አንጋፋው ጋሽ ስብሃት ገ---"መስማት አልቻልኩም።ተንቀጠቀጥኩ።ባለሁበት ቁጭ ብዬ ተንሰቀሰኩ።አነባሁ።አውነት አልመስልህ አለኝ።ለብዙ ደቂቃ ሳልቅስ ከቆየሁ በሁዋላ ወደ ቤት አዘገምኩ።የህልሙ ነገር አየገረመኝ ነው።የመንደሮቹ ገፅታ---የአርግብቷ ሁናቴ---ምን-ብቻ ወይ ስብሃት በጣም ይገርማል።አርግብቷ በርግጥም ታውቀዋለች።የሆነው ሁሉ ለተሾመ አጫውተዋለሁ።---ያው ትረካው ይፃፍ አንዳይለኝ አንጂ---
                       



                                         ተፈፀመ


                                                              12/06/2004
                                                                                ከናሙስ አ/ሀሊም
                               







No comments:

Post a Comment